Audiopedia Corona Campaign

ኮሮና ምንድን ነው? እራሳችንንስ ከቫይረሱ ለመከላከል ምን ማድረግ ይኖርብናል?

ኮሮና ቫይረስ ወይም ኮሮና ትንሽ ጀርም (ለአይን እንን ለማየት የማይቻል) ሲሆን በቀላሉ ከሰው ወደ ሰው ሊዛመትና ሰዎችን ለህመም የሚዳርግ ነው፡፡

ኮሮና ቫይረስ እንደጉንፋን ያለ ስሜት የሚያሳይ ሲሆን ደረቅ ሳል፣ የመተንፈስ ችግር፣ ትኩሳት እና ህመም ዋነኛ ምልክቶቹ ናቸው፡፡ ኮሮና የሚያጠቃው የመተንፈሻ አካላትን ነው፡፡ የሚያስከትለው ኢንፌክሽን ባብዛኛው አደገኛ የሚባል ባይሆንም ኒሞኒያ የሚባለውን የሳንባ በሽታ ግን ሊያስከትል ይችላል፡፡ ከዚህም ባሻገር የሰው ህይወትን ይቀጥፋል፡፡

ማንኛውም ሰው በኮሮና ሊጠቃ ይችላል፡፡ ኮሮና እድሜ ፣ ጾታ፣ ሀይማኖት፣ ቀለም፣ የሀብት ወይም የስራ ወይም የትምህርት ደረጃን አይለይም፡፡ ሆኖም ግን በእድሜ የገፉትንና በሌላ በሽታ ያለባቸውን ሰዎች ማለትም የመተንፈሻ አካል በሽታ፣ ስኳር፣ ወይም ካንሰር ያለባቸው በሽተኞች ለኮሮራ ቫይረስ በቀላሉ ተጋላጮች ናቸው፡፡

ኮሮና የሚተላለፈው በቫይረሱ ከተጠቃ ሰው በትንፋሽ በሚወጣ እርጥበት አዘል አየር ስለሆነ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ሲተነፍሱ፣ ሲስሉና ሲያስነጥሱ በቀላሉ እርጥበት አዘል አየሩ በሰው፣ በእቃ ወይም በምግብ ላይ ሊያርፍ ይችላል፡፡ ይህም ደግሞ ወደ ሰውነት አካል በአፍ፣ በአፍንጫና በአይን አማካኝነት ሊገባ ይችላል፡፡ አንዴ ወደ ሰውነት ከገባ በኋላ በሰውነት ውስጥ በቀላሉ የሚሰራጭ ሲሆን በሰውነታችን ውስጥ ምልክት ሳያሳይ ለ14 ቀናት ሊቆይ ይችላል፡፡ በመሆኑም ኮሮና የያዘው ሰው ምንም ምልክት ሳያሳይ ስለሚቆይ ለሌሎች በቀላሉ ሊያስተላልፈው ይችላል፡፡

በአሁኑ ግዜ ለኮሮና ክትባትም ሆነ መድሀኒት አልተገኘለትም፡፡ ኮሮና በአንቲ ባዮቲክ ወይም በባህላዊ መድሀኒቶች ሊሞት አይችልም፡፡ ኮሮና መከላከል የሚቻለው ከሰዎች ጋር ያለንን ንኪኪ በማስወገድና እጃችንን ቶሎ ቶሎ በመታጠብ ነው፡፡ ቫይረሱን ለመከላከል እጃችንን በሳሙናና በውሃ አዘውትረን መታጠብ ይኖርብናል፡፡ እጃችንን ለመታጠብ እጃችን ቆሽሾ እስክናየው መጠበቅ የለብንም፡፡ እጃችንንም ስንታጠብ ለ20 ሰከንድ በሳሙና ማሸት፣ በጥፍሮቻችንም የእጃችንን መሀል መፈተግ እና ሙሉ እጃችንን መታጠብ አስፈላጊ ነው፡፡ እጃችንን በሳሙናና ውሃ መታጠብ በአይናችን ያለየነውን እጃችን ላይ ያለውን ቫይረስ ሊገለው ይችላል፡፡ በመሆኑም እጆቻችንን አዘውትረን መታጠብ ሲኖርብን በተለይ ምግብ ከማዘጋጀታችን በፊትና በኋላ፣ መጸዳጃ ቤት ከተጠቀምን በኋላና ከመብላታችን በፊት መታጠባችንን መዘንጋት የለብንም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በሽተኞችን ከተንከባከብን በኋላ፣ እንሳቶችን ከነካን ወይም ካጸዳን በኋላ፣ ስንስል፣ ስናስነጥሰ ወይም አፍንጫችንን ካጸዳን በኋላ እጃችንን በሳሙናና በውሃ መታጠብ ይኖርብናል፡፡ እጆቻችን ብዙ ነገሮችን ይነካሉ በመሆኑም በቀላሉ የኮረና ቫይረስን ሊያገኙት ይችላሉ፡፡ አንድ ግዜ የተበከሉ እጆች ደሞ ቫይረሱን በአይን፣ በአፍንጫ እና በአፋችን በኩል ሊያስተላልፉት ይችላሉ፡፡ ከዚያም ቫይረሱ በቀላሉ ወደ ሰውነታችን ሊገባና ልንታመም እንችላለን፡፡


እራሳችንን ከቫይረሱ ለመከላከል ትኩሳትና ሳል ወይም ሌሎች የመተንፈሻ አካል ችግር ከሚታይበት ሰው ጋር መጠጋጋትና መነካካት አስፈላጊ አለመሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል፡፡ በምናስልበትና በምናስነጥስበት ወቅት አፋችንንና አፍንጫችንን በሶፍት ወይም በክርኖቻችን መሸፈን ይኖርብናል፡፡ የተጠቀምነውን ሶፍት ወዲያውኑ ክዳን ያለው ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ውስጥ መጣል ያስፈልጋል፡፡ ምራቃችንንም በየሜዳው ላይ መትፋት የለብንም፡፡ ከሰዎች ጋር በምንሆንበት ጊዜ ከአንድ እስከ ሁለት ሜትር ርቀን መቆምና መቀመጥ በቫይረሱ በቀላሉ እንዳንያዝ ያደርጋል፡፡ ምናልባት ሳል፣ ትኩሳት ወይም የመተንፈሻ አካል ችግር ያጋጠመውን ሰው ማገዝ የሚኖርብዎ ከሆነ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ማስክና የእጅ ጓንት ማድረግዎን በፍጹም መዘንጋት የለብዎትም፡፡ በተጨማሪም የእጆችዎን ንጽህና መጠበቅም ይኖርብዎታል፡፡

የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ተመራጩ መንገድ ከሰዎች ጋር ያለንን ንኪኪ ማስወገድ ነው፡፡ ኮሮናና ሌሎች ቫይረሶች በቀላሉ ከሰዎች ለሰዎች የሚተላለፉት በመጨባበጥ፣ በመተቃቀፍ ወይም በመሳሳም ነው፡፡ ስለዚህ ሰዎችን ሰላም ስንል ከአንገታችን ዝቅ በማለት እጅ በመንሳትና እጃችንን በማውለብለብ መሆን ይኖርበታል፡፡ በአካባቢዎ ኮሮና የሚኖር ከመሰለዎ ከሌሎች ጋር ላመገናኘት በቤትዎ እንዲቆዩ ይመከራል፡፡ በተጨማሪም የህመምና የጉንፋን ስሜት የሚሰማዎት ከሆነ እስኪሻልዎ ድረስ ከቤትዎ አይውጡ፡፡ ሆኖም የሚያስነጥስዎ ከሆነ፣ ደረቅ ሳል የሚያስሉ፣ ትኩሳት ካለዎት ወይንም መተንፈሻ አካልዎ ላይ የህመም ስሜት ካለዎት የህክምና እርዳታ ማግኘት ይኖርብዎታል አለበለዚያ ግን እስከ ሞት የሚያደርስዎ ችግር ሊያጋጥምዎ ይችላል፡፡ ስለኮረና የሚወሩ አሉባልታዎችና ትክክል ያልሆኑ እምነቶች በጣም አደገኛ ናቸው፡፡ ለምሳሌ አልኮልና እንደበረኪና ያሉ ነገሮችን መጠጣት ጠቃሚ ነው የሚባለው ከኮረናው የባሰ ለህይወት አስጊ ይሆናል፡፡ እርስዎ መስማትና ማድረግ የሚኖርብዎ ከጤና ባለሙያዎችና ከጤና ሚኒስቴርና ከመንግስት ባለስልጣናት የሚሰጠውን ምክር ብቻ መሆን አለበት፡፡

ይህንን መልእክት በተለያዩ መንገዶችና ማህበራዊ ሚዲያዎች ለምሳሌ በሃትስአፕ በማስተላለፍ ኮሮና እንዳይስፋፋ የራስዎን አስተዋጽኦ ያበርክቱ፡፡ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከልና ለማስወገድ በጋራ እንስራ! ይህ መልእክት የተላለፈው ኦዲዮፒዲያ በሚባል የጤና እውቀትን በሚያስጨብጥ አለም አቀፋዊ ፕሮጀክት ነው፡፡ ስለፕሮጀክቱ የበለጠ ለመረዳት የድርጅቱን ድረ ገጽ ይጎብኙ www.audiopedia.org